የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች እንዲሁም የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጎበኙ አዲስ አበባ፤ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበርና የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች ማህበር አባላት ቅዳሜ ጥቅምት 10 ቀን 2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጎብኝተዋል።እናትና አባት  አርበኞቹ የኢትዮጵያ አየርመንገድን ምስለ በረራ፣የጥገና ማዕከል፣ የካርጎ ማዕከል፣ አቪዬሽን አካዳሚ፣ ተርሚናል ማስፋፊያ እና እየተገባደደ ያለውን የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል የጎበኙ ሲሆን ከጉብኝቱ በኋላ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ስለ አየርመንገዱ እና የዕድገት ጉዞው ገለፃ ተደርጎላቸዋል።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖችአርበኞችማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ “ወጣት ሳለሁ በዲሲ 3 አውሮፕላን ከጅማ እመላለስ ነበር። አሁን ደግሞ በጀት አውሮፕላን የመሄድ እድሎ አጋጥሞኛል። ስነ-ስርዓቱን ስመለከት በየጊዜው እያደገና እየጠራ የመጣ በመሆኑ የሚያሳየው ይህንን ትልቅ ደርጅት ደከመን ሳይሉ ምንም ቀዳዳ ሳይኖረው እያስተናገዱ ስለመጡ ነው። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ አየርመንገድ በአለማችን ላይ በጣም የታወቀና ትርፋማ የሆነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች ማህበር ተወካይ ኮሎኔል እስጢፋኖስ ገብረመስቀል ለተዘጋጀው ጉብኝትና ገለፃ አየር መንገዱን ካመሰገኑ በኋላ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከትንሽ ወደ አለምአቀፍ አየር መንገድ ሲያድግ አይተናል፤ ምስክሮችም ነን። አየር መንገዳችን ብዙ ሥራዎችን ሰርቷል። በሰላማዊ ሥራም በጦርነት ጊዜም ሁለገብ እርዳታ ያደረገ አየር መንገድ ነው። ወደፊትም እድገቱ እየቀጠለ እንዲሄድ ምኞታችን ነው” በማለት የበኩላቸውን ሀሳብ አጋርተዋል።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች እና የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማህበራትበኢትዮጵያ አየርመንገድ እድገትና በአፍሪካ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በተቀዳጀው የመሪነት ሚና እጅግ መደሰታቸውንና መኩራታቸውን በመግለፅ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያምናለከፍተኛ አመራር አባላት ሜዳሊያዎችና ሌሎች ስጦታዎች አበርክተዋል።