የሃጂ ጉዞ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ለክቡራን ደንበኞቻችን የተሰጠ ማብራሪያ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በእስልምና እምነት እጅግ የተከበረውን አመታዊ የሃጅ ጉዞ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ለማገልገል በቂ ዝግጅት አድርጎ ሃጃጆችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። ሆኖም የሃጂ ጉዞ አስተባባሪ ኮሚቴ አስቀድሞ ከተጠየቀው የጉዞ መርሀ ግብር ተጨማሪ ሰሞኑን በሶማሌ ክልል በተከሰተው የጸጥታ ችግር ሳቢያ ለጉዞ ዘግይተው የመጡ ሃጃጆችን እና በሳዑዲ አየር መንገድ በተያዘላቸው የበረራ ምዝገባ መሰረት ሊስተናገዱ ባለመቻላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲያጓጉዝ ኮሚቴው ጠይቋል።ምንም እንኳን ወቅቱ ከፍተኛ የበረራ እንቅስቃሴ ያለበትና ሁሉም አውሮፕላኖቻችን በከፍተኛ በረራ የተጠመዱበት ወቅት ቢሆንም አየር መንገዱ ብሔራዊ ግዴታውን በማክበር ለሙስሊሙ ማህበረሰብ አገልግሎቱን አቅርቧል። 

በተጨማሪም ነሐሴ 08 ቀን 2010 ዓ.ም በነበረው መጥፎ የአየር ጠባይ እና ከባድ ዝናብ ሳቢያ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ብልሽት ገጥሞታል። በመሆኑም የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ በወቅቱ የነበሩ ገቢም ሆኑ ወጪ በረራዎችን ሙሉ በሙሉ ማስተናገድ ስላልቻለ አዲስ አበባ ማረፍ ከነበረባቸው በረራዎች ውስጥ ስድስቱ ጅቡቲ ለማረፍ ተገደዋል። የተቀሩትም ረዥም ጊዜ በአየር ላይ እንዲቆዩ ሆነዋል። በወጪ በረራዎችም ረዥም መዘግየት አጋጥሟል። በመሆኑም በዘገዩ በረራዎች ምክንያት ትራንዚት መንገደኞች ቀጣይ በረራዎችን እስከሚሳፈሩ ድረስ በርከት ወዳሉ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ሆቴሎች በመውሰድ ለማሳረፍ ተገደናል። ስለሆነም ከላይ በጠቀስነው ምክንያት ዘግይተው የደረሱ የሃጅ መንገደኞቻችንን በከተማው ውስጥ የሚገኙ ሆቴሎች ሙሉ በሙሉ በትራንዚት መንገደኞች ስለተያዙ የሃጅ መንገደኞቻችንን ወደ ሆቴል መውሰድ ባለመቻላችን በወቅቱ ይቅርታ ጠይቀናል።

ተጨማሪ ለሚደረገው በረራም ከሳዑዲ ሲቪል አቪዬሽን የበረራ ፍቃድ በመጠባበቅ ሂደት በመንገደኞች ማስተናገጃ በረራውን ለሚጠብቁ ሃጃጆች የምግብና መሰል መስተንግዶዎች በማቅረብና ተጨማሪ አውሮፕላን በመመደብ ሁሉንም የሃጂ ተጓዦች ወደ ጉዞ መዳረሻቸው አድርሰናል።

በዚህ አጋጣሚ ለሀጅ ተጓዞችና ሌሎች መንገደኞች በበረራዎች መዘግየት ለተፈጠረው መጉላላት ከልብ ይቅርታ መጠየቅ እንወዳለን።